የሰው ልጅ ኑሮ መሻሻል እና ሉላዊነት

ቬርኖን ስሚዝ

(በቬርኖን ስሚዝ) የዛሬው መልዕክቴ አዎንታዊ ነው፡፡ ወደ ስራ እንድንገባና የልዩ ሙያ ዕውቀት ባለቤት እንድንሆን ስለሚያስችሉን በፍቃደኝነት ስለሚደረግ ልውውጥና ገበያዎች ይመለከታል፡፡ የልዩ ሙያ ዕድገት መስፋፋት የሁሉ ሐብት ፈጠራ ምስጢርና ዘለቄታነት ያለው የሰው ልጅ መሻሻል ብቸኛ ምንጭ ነው፡፡ የሉላዊነትም (Globalization) ፅንሰ ሐሳብ ይኸው ነው፡፡

ፈተናው ሁላችንም በተመሳሳይ ጊዜ በሁለት ተደራራቢ የልውውጥ ዓለማት ላይ መስራታችን ነው፡፡

1)መጀመሪያ በሰጥቶ መቀበል (በሸጦ መግዛት) ላይ የተመሰረተ ግላዊና ማህበራዊ ልውውጥ በምናካሔድበት እንዲሁም በትናንሽ ቡድኖች ፣ በቤተሰቦችና በማህበረሰቦች ደረጃ የዓለምን ስርዓት በምንጋራበት  ዘመን ላይ መኖራችን ነው::

“ውለታህን እከፍላለሁ፡፡” የሚለው ሐረግ በሁለንተናዊነት በበርካታ የሰው ልጅ ቋንቋዎች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ሰዎች ለተደረገላቸው በጎ ተግባር በፈቃደኝነት ምስጋናቸውን የሚያቀርቡበት ነው፡፡ ከጥንት ጊዜያት ጀምሮ የነበረው ግላዊ ልውውጥ የልዩ ልዩ ሙያዎችን ዕድገት (የአደን ሙያን ፣ የፍራፍሬ ለቀማን ፣ የአደን መሳሪያ ስሪትን … ወዘተ) ፈጥሮ ለኑሮ ደህንነትና ለምርታማነት መሻሻል መሰረት ሆነ፡፡ ይህ የሙያ ክፍፍል ሰዎች በመላው ዓለም እንዲሰደዱ (እንዲሰራጩ) አደረጋቸው፡፡ ይህ የሚያሳየው ገበያዎች እራሳቸው ከመፈጠራቸው ረዥም ዘመናት በፊት ሉላዊነት በልዩ ሙያ መዳበር ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን ነው፡፡

2) ሁለተኛ የረዥም ርቀት ንግድ በማይተዋወቁ ሰዎች መካከል ተግባቦትንና የኅብረት ስራን ቀስ በቀስ እያጎለበተ በሚሔድ ፣ የግል ያልሆነ የገበያ ልውውጥ እየተካሔደ ባለበት ዓለም ውስጥ መኖራችን ነው::

አብዛኛውን ጊዜ ለሌሎች መልካም ነገሮችን የሚፈጥሩት ግላዊ የልውውጥ ድርጊቶቻችን ናቸው፡፡ በገበያ ስፍራ እያንዳንዳችን የግል ጥቅም ማግኘቱ ላይ ስለምናተኩር ይህ ሌሎች የመጥቀም ስሜት በውስጣችን አይኖርም፡፡

ይሁን እንጂ ቁጥጥርን መሰረት ያደረጉ የላቦራቶር ሙከራዎቻችን እንደሚያስረዱት የግል ጥቅማቸውን ለማሳደግ ሲሉ ወደ ህብረት ስራ የሚገቡና በትልቅ ገበያ ውስጥ ተግተው የሚሰሩት እነኚሁ ግለሰቦች ናቸው፡፡ በሚያደርጉት የግብይት እንቅስቃሴዎች ሳያውቁና ሳያቅዱ የቡድኑን አጠቃላይ የጋራ ጥቅም የሚያሳድጉትም እነዚሁ ሰዎች ናቸው፡፡ ለምን? ምክንያቱም የንብረት ባለቤትነት መብት መኖሩ ነው፡፡ በግላዊ ልውውጥ ውስጥ ገዢ የሆኑ ሕጎች በተሳታፊ ወገኖች ፍቃድ ከሚገኝ ስምምነት ይመነጫል፡፡ ግላዊ ባልሆኑም የገበያ ልውውጥ ውስጥ ገዢ የሆኑ ሕጎች ማለትም ሳይሰጡ መውሰድን የሚከለክል እንዲሁም   የንብረት ባለቤትነት መብት የመሳሰሉት በተቋማዊ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ተካትተው ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም ሁለቱም የልውውጥ ዓለማት በተመሳሳይ መንገድ የሚሰሩ ናቸው፡፡ እናም ለመቀበል መስጠት ይኖርባችኋል ማለት ነው፡፡

የብልፅግና መሰረት

የሐብት ፈጠራ መሰረት የሆኑት የሸቀጥና የአገልግሎት ገበያዎች ፣ በሙያ የመጠበብ ደረጃን ይወስናሉ፡፡ በተደራጁ ገበያዎች ውስጥ ያሉ አምራቾች የማምረቻ ወጪዎችን በአንፃራዊነት የመተንበይ ተሞክሮን ያዳብራሉ ፤ ሸማቾች በአንፃራዊነት በሚተነበይ ዋጋ የወጣላቸው ሸቀጣሸቀጦች አቅርቦት ይመራሉ፡፡ ሳይቋረጡ የሚከናወኑ እነዚህ የገበያ እንቅስቃሴዎች ለማመን በሚያዳግት ደረጃ በብቃት የሚሰሩ ናቸው ፤ የዘርፈ ብዙ ሸቀጣሸቀጦች ግብይት በሚካሔድባቸውና በጣም ውስብስብ የገበያ ትስስሮች ባሉበት ስፍራ ጭምር ሁሉ ብቃታቸው የሚደንቅ ነው፡፡ በገበያ ሙከራዎቻችን ያረጋገጥነው ሌላው ነገር ደግሞ ሰዎች የሚገዙትንና የሚሸጡትን ሸቀጣሸቀጦች (ዕቃዎች) ብዛትና የመጨረሻ መሸጫ ዋጋዎች መተንበይ የሚችል ሞዴል ይኖራል የሚለውን በአጠቃይ አይቀበሉም፡፡

በእርግጥ የገበያ ብቃት የተሳታፊዎች ቁጥር እጅግ መብዛት ፣ የተሟላን መረጃ ፣ የኢኮኖሚ ዕውቀትን ወይም በአይነቱ በጣም ልዩ የሆነ ዓለማዊ ጥበብን የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ከመነሻው ስናይ ሰዎች በገበያዎች ውስጥ የንግድ ስራን ሲያከናውኑ የነበረው ከረጅም ዘመናት በፊት አንድም የገበያን ሒደት የሚያጠና ኢኮኖሚስት ባልነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ በቃ የሚያስፈልጋችሁ ነገር ፣ በንግድ ስራችሁ ብዙ ገንዘብ ወይም አነስተኛ ገንዘብ እየፈጠራችሁ ባላችሁበት ጊዜ አሰራራችሁን የማሻሻል (የመቀየር) ዕድል እንዳላችሁ ማወቅ ነው፡፡ የሸቀጥና የአገልግሎት ገበያዎች ውበት ብዝሃነት ነው፡፡ የፍላጎት ማርኪያ አማራጮች ፣ የሰው ልጅ ሙያዊ ችሎታዎች ፣ የዕውቀት ፣ የተፈጥሮአዊ ሐብቶችና የአየር ንብረት ብዝሃነት።

የልውውጥ ነፃነት በሌለበት ፣ ብዝሃነት ድህነትን ያመላክታል፡፡ አንድ ሰው በአንድ ሙያ የተትረፈረፈ ፀጋ ቢሰጠው ወይም ተዝቆ የማያልቅ አንድ አይነት ሐብት ቢኖረው እንኳ ያለ ንግድ ከቶውንም መበልፀግ አይችልም፡፡ ሁላችንም በነፃ ገበያዎች አማካይነት በማናውቃቸው ፣ ልብ በማንላቸውና ወይም ከዚህም አልፎ በማንግባባቸው ሌሎች ሰዎች ላይ የተመሰረትን ነን፡፡ ይህ ዕውነት ነው፡፡ ገበያዎች ከሌሉ የቁስና የዕውቀት ድሃ እንሆናለን ፤ ኑሮአችንም የሰቆቃ ይሆናል ፤ እኛም ጨካኝ  እንሆናለን፡፡

ገበያዎች የኢኮኖሚ ልውውጥና የማህበራዊ መስተጋብር ስምምነታዊ ሕጎችን ተፈፃሚነት ይጠይቃሉ፡፡ ይህን ከዛሬ 250 ዓመት በፊት ዴቪድ ሂዩም ከተናገረው በላይ ጥሩ አድርጎ የገለፀ የለም፡፡ እንደ ዴቪድ ሂዩም ገለፃ ሶስት አይነት ተፈጥሮአዊ ሕጎች አሉ፡፡ እነርሱም የባለቤትነት መብት ፣ በስምምነት (በፈቃደኝነት) ማስተላለፍና ስምምነቶችን (ሕጎችን) ተፈፃሚ ማድረግ ናቸው፡፡ እነዚህ ገበያዎችን እንዲሁም ብልፅግናን መፍጠር የሚያስችሉ የስርዓት ዋነኛ መሰረቶች ናቸው፡፡

የሂዩም የተፈጥሮ ሕጎች ከጥንታዊው (ኦሪት) ዘመን ትዕዛዛት ይመነጫሉ፡፡ አትስረቅ ፣ የጎረቤትን ንብረት አትመኝና በሐሰት አትመስክር ከሚሉት የወጣ ነው፡፡ “የሥርቆት” ጨዋታ የሌላን ሰው ሐብት መቀራመት ያመጣል ፤ ሐብትን የማሳደግ ተስፋን ያጨልማል፡፡ የሌሎችን ንብረት መመኘት ፣ የሌላን ሰው ሐብትን አስገድዶ ለመከፋፈል ድርጊት ይጋብዛል ፤ ይህ ደግሞ የነገውን ምርት የማምረት ተነሳሽነት አደጋ ውስጥ ይከታል፡፡ በሐሰት መመስከር ማህበረሰብን ያዋርዳል ፤ የአስተዳደርን ተአማኒነት ፣ የኢንቨስተርን አመኔታ ፣ የረዥም ጊዜ የትርፋማነትን ዕቅድና ግላዊ ልውውጦችን ዝቅ ያደርጋል ፤ ይህ ደግሞ የሰብአዊነት መገለጫዎችን ይበልጥ ያጎድፋል፡፡

(ይህ ጽሁፍ Human Betterment through Globalization በሚል ርዕስ ቬርኖን ስሚዝ እኤአ በ2005ዓ/ም የጻፈው ነው። ቬርኖን ስሚዝ ካሊፎርኒያ በሚገኘው ቻፕማን ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪ ሲሆን እኤአ በ2002 የኖቤል ሽልማት አግኝቷል።ጽሁፉ ወደ አማርኛ የተመለሰው በአሳታሚው ፈቃድ ነው።)

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.