ስቴፋኒ ሂሞኒዲስ፡ ኢንተርፕርነር ዕውቅ ዲጄ እና ጋዜጠኛ

stha“መሆንና ማግኘት የምፈልጋቸውን አልማለሁ፡፡እስካሁን ድረስም አልሜ ያጣሁት አንዳች የለም፡፡በእርግጥ ስኬታማ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ዋጋ መክፈሉ የማይቀር ነዉ፡፡” የምትለው ስቴፋኒ ሂሞኒዲስ ሜክሲኮ ውስጥ በ ዩኒቪሲዮን ራዲዮ KSCA La Nueva 101.9 FM ስመጥር ዲጄ ናት፡፡ “የወንድ ጓደኛየን እና ቤተሰቦቸን ጥየ ነው የተሰደድኩት፡፡ከህልሜ በቀር አብሮኝ ማንም አልነበረም፡፡በዚያ ደግሞ አልተከፋሁም፡፡” ትላለች፡፡

ስቴፋኒ ጎበዝ የራዲዮ ወይንም የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ መሆን ነበር የምትፈልገው፡፡ቤተሰቦቿ ግን ሐኪም መሆን አለባት በማለት የህክምና ት/ቤት ለማስገባት ላይ ታች ብለው የመግቢያ ፈተና እንድትፈተን አድርገዋታል፡፡ ያም ሆኖ ለቤተሰቦቿ የኮምዩኒኬሽን እና የጋዜጠኝነት ትምህርት ማጥናት እንጅ ፈጽሞ ሐኪም መሆን እንደማትፈልግ ስትነግራቸው እናቷ “ባል ማግባት አለብሽ-የምትፈልጊው ባል ነው አይደል?” ያሏትን በማስታወስ ፈገግታዋን አስቀድማ “ቀስ በቀስ ሁሉም የእኔን ሃሳብ ደገፈ፡፡” አለች፡፡

እንደ እድል ሆኖ የኮምዩኒኬሽን እና የጋዜጠኝነት ትምህርቷን በጓዳላሃራ ዩኒቨርስቲ በመከታተል ላይ ሳለች ከ Nuclo Radio Guadalajara ጋር ቃለመጠይቅ ያደረገችው ስቴፋኒ በ1999 ዓ/ም ይህንኑ ሬዲዮ ጣቢያ ለመቀላቀል ችላለች፡፡ ከዓመት በኋላ የ CBS ን ተወካይ ለማግኘት በመቻሏ ካሊፎርኒያ ፍሮንሶ ዉስጥ በ CBS Radio’s VIVA 106 FM ዲጄ ሆና ለመስራት እድሉን አገኘች፡፡

“ቁንጥንጥ ባህሪ ነበረኝ፡፡ከሰው ጋር መግባባትን በተመለከተም እስከዚህም ነኝ፡፡” ስቴፋኒ ፍሮንሶ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል ይህን ባህሪዋን መቀየሯንና ባብዛኛው ገበሬዎችና ሕገወጥ ስደተኞች የሆኑ የፍሬንሶ ነዋሪዎች ጋር መገናኘቷን ትናገራለች፡፡ “ይህ ደግሞ ምሉዕ አድርጎኛል፡፡ ሰዎች ሁሌም ራሳቸውን እንዲችሉ እተጋለሁ፡፡በተለይ ደግሞ ሴቶች፡፡”

ስቴፋኒ የ CBS ሬዲዮ ጣቢያ የእሷን መርሃ ግብር አጥፎ ከስራ እንዳሰናበታት ለአንድ አሮጌ መኪና ለሚሸጥ ድርጅት አፈቀላጤ ሆና ሰርታለች፡፡ ስቴፋኒ ይሄን ጊዜ ስታስታውስ ደስ አይላትም፡፡

“የነበረኝን ህልም ምን ዋጠው? እንዴት ራዕዬን አጣዋለሁ? ለብዙ ጊዜ አብሮኝ የኖረው ራዕየ የት ገባ?” በማለት ራሷን ደጋግማ የጠየቀችው ስቴፋኒ በ 2004 ዓ/ም ሳንዲያጎ ከተማ በሚገኘው እና በ Univision ራዲዮ ጣቢያ ስር በሚገኘው Viva 102.9 FM ለመቀጠር ችላለች፡፡ይህ ሬዲዮ ጣቢያ በአሜሪካን ሃገር ከፍተኛ ተደማጭነት ያለው ሲሆን የስርጭት ቋንቋውም የስፓኒሽ ነው፡፡

በስቴፋኒ እምነት ኢንተርፕርነር ማለት “ህልም ያላቸው እና ሁልጊዜ ከእንቅልፋቸው ሲነቁ ያን ህልማቸውን እውን ለማድረግ የሚታትሩ ሰዎች ማለት ነዉ፡፡ ትላልቅ ህልሞቼ ሁሉ በውስጤ የሆነ ነገር ፈጥረዉልኛል፡፡ያ ነገር ደግሞ ወደህልሜ የሚወስደኝ መንገድ ወይም እልህ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ወድቄ ተስፋ ልቆርጥ ስል ከወደቅሁበት የሚያነሳኝ በውስጤ ያለው ህልም የሰጠኝ ብርታት ነዉ፡፡ ‘እኔ ማነኝ? ምንድነው መሆን የምፈልገው?’ እያለ ከማሰብ እንዳልቦዝን ያደርገኛል፡፡ስኬታማ ያደረገኝ ብርታቴ!”

ስቴፋኒ መርሃ ግብሮቿን በቀን ለማስተላለፍ ባላት ፍላጎት በምትሰራበት ተቋም ስር ላለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሪፖርተር ሆና ለመስራት ያስገባችው ማመልከቻ ወዲያው ተቀባይነት አግኝቶላታል፡፡ ፍሬንሶ ዉስጥ ያጣችውን ስራ እዚህ በማግኘቷ ደስተኛ የሆነችው ስቴፋኒ “ይህ የተሣካው አንዱ ትልቁ ህልሜ ነዉ፡፡” ትላለች፡፡

በ2008ዓ/ም ሁለት የኤሚ/Emmy ሽልማትን የተቀበለችው ስቴፋኒ ይህ ሲሆን እድሜዋ ገና ሃያ ስድስት/26 ዓመት ነበር፡፡ “ህልሞቼ ስኬታማ በመሆናቸው ዛሬ በሌላ ህልም ተተክተዋል፡፡” የምትለው ስቴፋኒ ሳቅ ወጓን ካቋረጣት በኋላ “አሁን የምፈልገው ስቴዲየም መሃል ቆሜ በሺሕዎች ለሚቆጠሩ ሴቶች ህልማቸውን እንዴት ዕውን ማድረግ እንደሚችሉ ንግግር ማድረግ ነው፡፡” ስትል ትቀጥልና “ወር እየጠበቁ ደሞዝ ከመቀበል ያለደሞዝ ህልምን መከተል እንደሚቻልና እንደሚሻልም ጭምር አስተምራለሁ:: ለዚህ ደግሞ ለህልምህ ዕውን መሆን መትጋት እና ጠንክሮ መስራት ብቻ ነው የሚጠበቅብህ፡፡ ገባህ?
እኔ ሪፖርተር ሆኜ መስራት እፈልግ ነበር፡፡ በርግጥም ሆኛለሁ፡፡ስርጭቱን በስፓኒሽ ቋንቋ ባደረገው ግዙፉ የሬዲዮ ጣቢያም መስራት ምኞቴ ነበር፡፡ እየሰራሁ ነው፡፡ ነገሮች አይሆኑም ብለው ለሚዳከሙና ለማያምኑ ሁሉ ትምህርት ብሰጥ ደስተኛ ነኝ፡፡አሁን እንደነገርኩህ አዳዲስ ህልሞች አሉኝ፡፡ግን እነሱን ተግባራዊ ለማድረግ ዘልየ አልገባም፡፡ምክንያቱም ህልሞችህን ዕውን ከማድረግህ በፊት ማብላላት ማሰብ እና ማስላት ይኖርብሃል፡፡” ስትል በርግጥም የተኛን ታነቃለች ወ/ሪት ስቴፋኒ፡፡

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.