ጃክ ካንፊልድ: ኢንተርፕርነር፣ደራሲ እና The Canfield Training Group ሊቀመንበር

“የምፈልገውን ነገር መሥራት፤የምሻውን ነገር ማግኘት እፈልግ ነበር፡፡አሁን ሁሉም ዕውን እየሆኑልኝ ስለሆነ ማድረግ የምፈልገውን እና እንዲኖረኝ የምፈልጋቸውን ነገሮች የእኔ የማድረግ አቅም አለኝ፡፡” የሚለው ጃክ ካንፊልድ የሕይዎት ፍልስፍናው “ራዕይና ህልም ይኑርህ፤ከዚያም እውን እንዲሆን ጥረት አድርግ” የሚል ነው፡፡

በጃክ አመለካከት ማንኛውም ራዕይ ያለውና ለዚያ ራዕዩ እውን መሆን የሚታትር ሰው ኢንተርፕርነር ነው፡፡ጃክ እንዲህ ይላል “ብዙ ሰዎችን እያቸው፡፡የሆነ አንድ ሰው ጨዋታ  እስኪፈጥር ይጠብቃሉ፡፡እነዚህ ሰዎች ያን ጨዋታ ለመጫወት ፍላጎታቸው ይህ ነው አይባልም፡፡ለምሳሌ ጨዋታው እግር ኳስ ቢሆን እግር ኳስ ለመጫወት እንጅ እግር ኳስ ስለሚጠይቀው የቡድን ስራ ምንም አይጠይቁም፡፡ ያለ ቡድኑ አባላት ቅንጅት ደግሞ ውጤታማ ቡድን መገንባት አይቻልም፡፡ ጃክ ቀጠል አድርጎም ራዕይና ህልምህ ዕውን የሚሆኑት ግን የራስህ የሆነ አንድ ቢዝነስ በመጀመር ወይም ስለምትሰራው/ስለምታደርገው/ስለምትጫወተው ነገር የጨዋታውን ሕግ ስታውቅ ነው፡፡”

ጃክ በስድስት/6 ዓመት እድሜው በእድሜ ለገፉ አሜሪካዊያን ወይዛዝርቶች የመጠጥ ውሃ እመንደሩ ከሚገኙ ሱፐር ማርኬት በእየቤታቸው በማድረስ ነበር ቢዝነስ የጀመረው፡፡

“በሰባት/7 ዓመቴ ከሚገባው በላይ ሃብታም ሆንኩ::” ሲል ከጃክ ፊት ላይ የተለመደው ፈገግታ አሁንም በግልጽ ይነበባል፡፡ 

ጃክ ስለ ለውጥና ስኬት ሥራዬ ብሎ ማውጠንጠን የጀመረው በ 1966 ከሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ተመርቆ ኢነር ሲቲ/Inner-City ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሚያስተምርበት ጊዜ የክሊሜንት(W.Clement) ተቋም በዚያ በሚያዘጋጀው ጤናማና ትክክለኛ የአይምሮ እድገትን አስመልክቶ በተሰጠ ወርክሾፕ ላይ በተካፈለበት ወቅት ነበር፡፡

ከዚህ በኋላ ጃክ ከራሱ ልምድና እውቀት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸውን በሥነ ልቡና በራስ መተማመን እና በራስ ተነሳሽነት ላይ የሚያጠነጥን ፕሮግራም በመቅረጽ ለተግባራዊነቱ ደፋ ቀና ማለት ጀመረ፡፡

 Insight Training Seminars የተባለው ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት በሚያዘጋጀው የግለሰብን እና የባለሙያዎችን ብቃት የሚያዳብር ዝግጅቶች ላይ በማስተማር የቀረጸውን ፕሮጀክት/ፕሮግራም ትክክለኛነት ያረጋገጠው ጃክ ፤በ 1983 እ.ኤ.አ የራሱን ድርጅት አቋቋመ፡፡

ጃክ ልምዱን እና እውቀቱን ፈትሾ ያረጋገጣቸውን እና ስኬታማ የሆነባቸውን የትምህርት ፕሮግራሞቹን በይበልጥ ለሌሎች ለማዳረስ በሚል ያቋቋመው ድርጅት ዘ ካንፊልድ ትሬኒንግ ግሩፕ/ The Canfield Training Group/  ይባላል፡፡

“ሁሌ ያለፍኩባቸውን የስራ ጊዜያት ዞሬ ስመለከታቸው የሚታየኝ ዋና ነገር ቢኖር የሆነ ነገር በምፈልግበት ወቅት ወደምፈልገው ነገር መሄዴ ነው፡፡” በማለት በከፍተኛ የራስ መተማመን መንፈስ የሚናገረው ጃክ አርአያዬ የሚላቸው ሁለት ሰዎች ወላጅ አባቱን እና የእንጀራ አባቱን ሲሆን “እነዚህ ሰዎች ሁሌ የሚፈልጉትን ለማግኘት ይታትሩ ነበር፡፡ ግን ብዙ ጊዜ አይሳካላቸውም ነበር፡፡እንዲያውም አልፎ አልፎ ይወድቁ ነበር፡፡ነገር ግን ሁሌም ይጥራሉ፡፡በእውነት ይሄ ለኔ በውስጤ ትልቅ መነቃቃትን ብርታትን እና መነሳሳትን ነው የፈጠረብኝ፡፡” ይላል፡፡ 

መነቃቃትን መነሳሳትን እና ብርታትን ለሌሎች ማጎናጸፍ ደግሞ የጃክ የሕይወት ዘመን ርዕይና ግብ ናቸው፡፡

“እነዚህ ሁሉ ለኔ እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡እነዚህ ርዕዮች ከሌሉን እኮ ሁላችንም ቢሆን በዚህ በአስቸጋሪና በውጣውረድ በተሞላ ዓለም ውስጥ ቀጣይነታችን ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፡፡” የሚለው ጃክ ከዚህ እምነቱም አንድም ቀን ውልፊት ብሎ አያውቅም፡፡ “የውድቀት ፈተናን ፊትለፊት ትግል በገጠምኩበት ወቅት እንኳ እኒህ ርዕዮቼን ፈጽሞ ለውጬ አላውቅም፡፡ለዚህም ምስክሮቼ The Chicken soup በሚል ርዕስ የጻፍኳቸው መጽሃፎቼ የተጎናጸፉት ስኬት ነው፡፡” በማለት ስለስኬቱ በኩራት ይናገራል፡፡ 

በ1991 ዓ/ም አንድ ድንገተኛ ሃሳብ ብልጭ ያለለት ጃክ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ማውጣት ማውረድ ያዘ፡፡

“ለምንድነው የሰማኋቸውን እና እራሴ ጭምር ያስተማርኳቸውን ለለውጥ የሚያነሳሱ ታሪኮች በጥራዝ ሰብስቤ የማላሳትማቸው? ሰው አንብቧቸዋል?” 

በእርግጥ ጃክ ታሪኮቹ በተለያየ ጊዜ ወጥተው አንባቢዎቹን ወዳሰቡበት የለውጥ ጎዳና እንዲገቡ እና በችግር ወቅት ጠንካራ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ 

ጃክ ይህን ሃሳቡን ለጓደኛው ለማርክ ቪክቶር ሃንሰን ሎስ አንጀለስ ውስጥ ቁርስ ጋብዞ ካማከረው በኋላ ለመጀመሪያው Chicken soup for the Soul የሚሆኑ አጫጭር የማነቃቂያ ጽሁፎችን አቀናበሩ፡፡ ከዚያም ወደ ኒውዮርክ በመብረር ለሶስት ቀናት በቀን ለስምንት ጊዜያት ያህል ጉባዔ/ስብሰባ እያዘጋጁ መጽሃፉን አስተዋወቁ፡፡ በእነዚህ ሶስት ቀናት በተካሄዱ ዝግጅቶች ተካፋይ የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች ደስተኛ እንዳልነበሩ የተረዳው ጃክ በመቀጥል ጥራዛቸውን በእጃቸው ይዘው በየዓመቱ በሚካሄደው የአሜሪካ የመጽሃፍ ኤክስፖ ላይ በመገኘት በመቶዎች ከሚቆጠሩ አሳታሚዎች ጋር መነጋገር ችለዋል፡፡ነገር ግን ያናገሯቸው አንድ መቶ አርባ አራት/144 አሳታሚዎች በሙሉ ስራቸውን አጣጥለው ፊት በመንሳት ነበር የሸኟቸው፡፡

እንደ እድል ሆኖ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ሄልዝ ኮምዩኒኬሽን/Health Communications Inc./ የተባለ አነስተኛ አሳታሚ ኩባንያ በመጽሃፉ ይዘት ላይ እምነት ስላደረበት ድንገተኛ እና ፈጣን ውሳኔ በማድረግ መጽሃፉን ለማሳተም ተስማማ፡፡

ይህን ተከትሎ ጃክና ማርክ መጽሃፋቸው በደንብ እንዲሸጥላቸው በመጀመሪያ አምስት የመጽሃፍ ቅጅዎችን ለሬዲዮ ጣቢያዎች በመላክ የቃለ መጠይቅ ቀጠሮ እንዲያዝላቸው ሆነ፡፡ በየመድረኩ ንግግር ማድረግ የተለያዩ ጽሁፎችን በየጋዜጣው መጻፍ እና ስለስራቸው መግለጫ መስጠትም የማይዘነጋ እና ተከታታይ የየዕለት ተግባራቸው ሆነ፡፡

ይህን ሁሉ እያደረጉ እንኳ የመጀመሪያው Chicken soup መጽሃፍ የከፍተኛ ሽያጭ ጣራ ደርሶ መመዝገብ የቻለው ከ አስራ አራት ወራት በኋላ ሲሆን  “ከዚያ በኋላ የሆነው ግን ለማመን ይቸግር ነበር፡፡” ይላል ጃክ፡፡

“እንግዲህ በዚህ ፍጥነት ነው ሁለት መቶ ሃያ አምስት/225 ርዕሶችን የያዙት ሰባቱ  Chicken soup መጽሃፎች አንድ መቶ ሃያ አምስት ሚሊዮን ኮፒ የተሸጡት፡፡ እንዲያውም በአንድ ወቅት በአንድ ቀን ሰባቱም በ ኒውዮርክ ታይምስ የመጽሃፍ ሽያጭ ጣራ መመዝገቢያ ገጽ ላይ ቁንጮ ሆነው በመስፈራቸው በ ጊነስ ቡክ ኦፍ ወርልድ ሪኮርድስም ለመመዝገብ በቅተናል፡፡መጽሃፎቹ ከአርባ/40 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች ተተርጉመው በመላው ዓለም ብዙ ሚሊዮኖችን ለለውጥ እንዳነሳሱና እንደለወጡ አሁንም ለብዙዎች ተስፋ እየሰጡ እንዳሉ  አውቃለሁ፡፡” የሚለው ጃክ “በውስጤ ያለው ህልም አሁንም ሌሎችን ማጠንከር ማበርታት እና ከፈተና ጋር ተጋፍጠው የሚያልፉ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ለዚህ ደግሞ የኔ ድርጅት በመላው ዓለም ከተለያዩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ጋር እየሰራ ይገኛል፡፡ለማናቸውም ቢሆን ካሉበት ቦታ ወደሚፈልጉት ቦታ እንዴት እንደሚሄዱ ያሳያቸዋል፡፡”

ጃክ በ2004 ዓ/ም ከደራሲዎች ከንግግር አቀናባሪዎች እና ከእውቀት መሐንዲሶች ጋር በመሆን የለውጥ እና የአመራር ጉባዔ የጀመረ ሲሆን ይህ ጉባዔ የግለሰቦችንና የባለሙያዎችን ክህሎትና ብቃት በማጎልበት ረገድ ለዓለም የበኩሉን አስተዋጽዖ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡

ይህ ጉባዔ የተለያዩ ሰዎችን እርስ በርስ በማገናኘት የየራሳቸውን ተሞክሮ እንዲጋሩ ከማድረጉም በላይ የጃክ የእድሜ ልክ ህልም የሆነውን ሌሎች ራዕያቸውን እንዴት መፍጠር እንደሚችሉ በማስተማር እና ይህንኑ እውን እንዲያደርጉ በማበረታት ረገድ ወሳኝ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ የዚህ ጽሁፍ አንባቢ ከሆኑ ራዕይዎን ለመፍጠር አሁኑኑ ማሰብ ይጀምሩ፡፡ ከዚያም ወደ ራዕይዎ ይራመዱ፡፡ 

 

Advertisement

One thought on “ጃክ ካንፊልድ: ኢንተርፕርነር፣ደራሲ እና The Canfield Training Group ሊቀመንበር

  1. Pingback: ጃክ ካንፊልድ: ኢንተርፕርነር፣ደራሲ እና The Canfield Training Group ሊቀመንበር | tmuv

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.