ናንሲ ኦሴይ:ኢንተርፕርነር እና የዓለማቀፉ ሜዲካል ኮርፕስ ፕሬዚዳንት

ናንሲ ኦሴይ የተወለደችው ሲዳር ራፒድስ/አይዋ ግዛት ውስጥ በሃገረ አሜሪካ ነው፡፡ከልጅነቷ ጀምሮ ሥራ በጣም ትወድ እንደነበር የሚያውቋት ሁሉ ለመናገር ሰንፈው አያውቁም፡፡ናንሲ ዛሬ በዓለም ላይ ትልቅ ሊባል የሚቻለውን የሰብዓዊ እርዳታ የሚለግስ ድርጅት የምታስተዳድር ሲሆን ይህ ድርጅት ከሃምሳ በላይ በሚሆኑ አገራት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የገንዘብና የጤና እንክብካቤ እርዳታ ያደርጋል፡፡

 በ1986ዓ/ም ስራውን ከሶስት በማይበልጡ ሠራተኞች የጀመረው ሜዲካል ኮርፕስ  (Medical Corps) የተባለው ድርጅቷ በ2009 ዓ/ም ራሱን በማጠናከር ዓለማቀፋዊ ሥራውን አሃዱ ያለው የ አንድ መቶ ሃያ አምስት ሚሊዮን ዶላር/150,000,000/ በጀት በማጽደቅና ከሶስት ሺሕ አምስት መቶ/3500/ በላይ የሚሆኑ የበጎ ፍቃድ ሰራተኞቹን በማሰማራት ነበር፡፡  

ናንሲ በበኩሏ በራስ ተነሳሽነት ቢዝነስን መጀመር ወይም አዲስ ነገር መክፈትን በሚመለከት ዋናው ተፈላጊ ነበር ጥረት እንጅ ሌላ አይደለም ባይ ነች፡፡

“ጥረትህ ወይ ወደፊት ይወስድሃል ወይ ካሰብከው ሳያደርስህ ይከድሃል ወይ ባለህበት ሊያሴድህ ይችል ይሆናል፡፡ብዙ ጊዜ ግን ጥረት ካደረግህ ሶስት እርምጃ ወደፊት አንድ እርምጃ ወደኋላ እንደገና ሁለት እርምጃ ወደፊት መሄድህ የማይቀር ነው፡፡ታዲያ ሁሌም ወደ አላማ የሚወስድህን መንገድ ለአፍታም መዘንጋት የለብህም፡፡ምክንያቱም ብዙ ሰዎች ራዕያቸውን ዕውን ለማድረግ ጉዞ ከመጀመሩ በኋላ ‘ግን ባይሳካስ’ እያሉ ፊታቸውን ከራዕያቸው በማንሳታቸው እና ወደኋላ በመመልከታቸው ወድቀዋል፡፡የእነዚህ ሰዎች የውድቀት ውድቀት ደግሞ ከውድቀታቸው ለመነሳት አለመሞከራቸው ነው፡፡” ትላለች-ናንሲ፡፡

ለናንሲ ትልቁ ድል በመላው ዓለም የሚገኙ ትርምስና ሁከት የነገሰባቸው አካባቢ ነዋሪዎችን የመድሃኒት እርዳታ እንዲደርስ ማድረጓና የጤና እን/ክብካቤ ስልጠና መስጠት መቻሏ ነው፡፡

“ጥረታችን ፍርሃት እንኳ ሊያሸንፈው ባለመቻሉ ተሳክቶልናል፡፡ፍርሃታችንን ያሸነፈው ደግሞ ጥረታችን ነው፡፡ይህ ባይሆን ኑሮ ገና ድሮ በመጀመሪያው ዘመቻችን ወቅት በአንጎላ በሶማሊያ እና በአፍጋኒስታን ወድቀን እንቀር ነበር፡፡ጥረታችን ፍሬ በማፍራቱ ዛሬ ግጭትና አመጻ ባለባቸው እንደ ዳርፉር፣ ሰሜናዊ ኡጋንዳ፤ ዲ.ሪ.ኮንጎ፣ላይቤሪያ፣ችችኒያ፣ኢትዮጵያና ኢራቅ ውስጥ ከበጎ ፈቃድ ሰራተኞቻችን ጋር ሆነን እየሠራን ነው የምንገኘው፡፡”

ናንሲ ቀጠል በማድረግም “ሁላችንም ልናስበው ከምንችለው በላይ መከራ ውስጥ ያለን እና ሰብዓዊ ክብሩ ጭምር የተገፈፈበት ማህበረሰብ ከዚህ ስቃይ የሚገላገልበትን መንገድ በመቀየሳችን ሲያገግሙ እና እንደገና ሰው ሲሆኑ በዓይናችን እያየን ነው፡፡ይህ ደግሞ ተደጋገመ መሰለኝ እንጅ አሁንም የእልህ አስጨራሽ ጥረታችን ውጤት ነው፡፡”

ናንሲ ችግርን ከማማረር ይልቅ ትማርበታለች፡፡በጨለማ ውስጥ ሆና እንኳ ብርሃንን መፈለግ አታቆምም፡፡ ከችግርና ከመከራ ሽሽትም ፈጽሞ ከመንገዷ ለመሄድ ወጥታ አታውቅም፡፡ለዚያ አስረጅው ደግሞ እራሷ ናት፡፡

“ወደ ሶማሊያ ገብቶ ለመሥራት ‘ኢንተርናሽናል ሜዲካል ኮርፕስ’ የመጀመሪያው አሜሪካዊ ድርጅት ነው፡፡እዚያ ያለው የችግርና የመከራ ስንክሳር ይሄ ነው አይባልም፡፡ሆኖም ሶማሊያ ውስጥ ገብቶ ለመሥራት አላገደንም፡፡ይህን በአመጻና በጦርነት  የተቀፈደደ ህዝብ እንዴት ልንረዳው እንደምንችልና በአስቸጋሪው የሶማሊያ መልክዓ ምድር እርዳታችንን እንዴት ልናደርስለት እንደምንችል ዘዴዎችን ለማፈላለግ ብዙ መጨነቃችን አልቀረም፡፡” የምትለው ናንሲ “በሺሕዎች የሚቆጠሩ እንቅፋቶችና ወጥመዶች እዚህም እዚያም ባሉባት ሶማሊያ ማንም ለማሰብ እንኳ የሚከብደውን በጎ ተግባር እያከናዎንን የምንገኘው ችግርና መከራን መሸሽ እና ማፈግፈግ እኛ ዘንድ ቦታ ስለሌለው ነው፡፡”  ብላለች፡፡

 በ1986ዓ/ም ‘ኢንተርናሽናል ሜዲካል ኮርፕስ’ን ስትቀላቀል ገና ጨቅላ የነበረ ድርጅት ሲሆን እሷም የሁለት ዓመት የስራ ልምድ ብቻ ነበራት፡፡ ያኔ የሃያ ሰባት ዓመት ዕድሜ የነበራት ናንሲ ይህን ምግባረ ሰናይ ድርጅት የተቀላቀለችው በጣም ጎበዝ የሆኑ፣ አዲስ ነገር ለመፍጠር ዘወትር የሚተጉ እና ሌሎችንም ለማገዝ ብርቱ ጥረት የሚያደርጉ ወጣቶች የነበሩበት ስለነበር እንደሆነ ትገልጻለች፡፡

ትልቅ ራዕይና ግብ የነበሩት ጨቅላው ‘ኢንተርናሽናል ሜዲካል ኮርፕስ’ ም ዛሬ በመላው ዓለም አንቱታን ያተረፈ ትልቅ የሰብዓዊ እርዳት የሚሰጥ ድርጅት ሆኗል፡፡ከልጅነቴ ጀምሮ ወላጆቼ ሥራ እንድወድ አድርገውኛል የምትለው ናንሲ በወላጆቿ የበቆሎ እርሻ ውስጥ ተፍ ተፍ ትል እንደነበርም ትናገራለች፡፡

በአይዋ የበቆሎ እርሻ ውስጥ ስትቦርቅ ያደገችው ናንሲ ከአመጽ ሁከትና ችጋር ጋር ተናንቀው በመላው ዓለም መራራ ሕይዎትን ከሚመሩ ሰዎች በተጨማሪ በ2004 ዓ/ም በ ሱናሚ የባህር ውስጥ ነውጥ ሕይዎታቸው የተመሣቀለውን ኢንዶኒዥያዊያን እንዲሁም በ2010 ዓ/ም በደረሰባቸው አስከፊ የመሬት መንቀጥቀጥ የተጎዱ ሃይቲያዊያንን በኢንተርናሽናል ሜዲካል ኮርፕስ በኩል እርዳታ በመስጠት ባታስቦርቃቸውም እሷና ድርጅቷ የቻሉትን ያህል ከጎናቸው እንደሚቆሙ በዓይናቸው አይተዋል ፡፡እያዩም ነው፡፡

ናንሲ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ ግዙፍ የሰብዓዊ እርዳታ ለጋሽ ድርጅቶች ጋር አማካሪ በመሆን አብራቸው ትሰራለች፡፡ ከነዚህም መካከል የዓለም የጤና ድርጅት፣ዩኒሴፍ፣የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና የአሜሪካ መንግስት የሰብዓዊና የጤና አገልግሎት ዲፓርትመንት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ናንሲ ከስራዋ ጋር በተየያዘ ለአሜሪካ መንግስት ኮንግረስ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትና ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ልምዷን ምስክርነቷን እና እውቀቷን አካፍላለች፡፡በማካፈል ላይም ትገኛለች፡፡

 

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.