ኢንተርፕርነር እና የካፔሎ ካፒታል ግሩፕ ሊቀመንበር-አሌክሳንደር ካፔሎ

Image

በአስራ ሰባት ዓመት እድሜው የመጀመሪያ ዓመት የኮሌጅ ተማሪ ሳለ ነው የኢንቨስትመንት ባንክ በመክፈት የቢዝነሱን ዓለም የተቀላቀለው፡፡ሆኖም ግን ከልጅነቱ ጀምሮ ሥራ ሳይንቅ ያገኘውን ሥራ ሁሉ ይሠራ ነበር፡፡ካሊፎርኒያ ግዛት ቤከርፊልድ የተወለደው የካፔሎ ካፒታል ግሩፕ ሊቀመንበር-አሌክሳንደር ካፔሎ፡፡

የካፔሎ ግሩፕን በ1973 ከከፈተ በኋላ እየሰራ የሚገኘውን የቢዝነስ ዓይነት ለይቶ ያወቀው ዘግይቶ ነበር፡፡ “እርግጥ ነው ምን ዓይነት የባንክ ቢዝነስ ውስጥ እንዳለሁ እና ኢንቨስትመንት ባንኪንግ እንደሚባል የተረዳሁት በጣም ዘግይቼ ቢሆንም ይህን አለማወቄ ግን ሥራውን እንዳልሠራ አላደረገኝም፡፡” የሚለን አሌክስ ካፔሎ ነው፡፡

በደቡባዊ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ሁለት አስተማሪዎቹ አሌክስ ፍላጎትና ህልሙን ለማሳካት ይችል ዘንድ ኤስቢኤ/SBA/ በሚባል የኢንተርፕርነሮች አስተዳደር ተቋም ውስጥ የሥራ ላይ ልምምድ እንዲያደርግ አመቻችተውለታል፡፡ በዚህ ተቋም በሚያሳየው ትጋት እና ቅልጥፍና አስተማሪዎቹን ያላሳፈረዉ አሌክስ በመምህሮቹ እገዛ የባንክ ስራ ለመጀመር የሚያስችለውን የቢዝነስ እቅድ አዘጋጀና ዘ ካፔሎ ግሩፕን/The Capello Group/ መሰረተ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አሌክስ የተለያዩ ኩባንያዎችን በማማከር ቢዝነስና እቅድን ለማሳካት የሚረዱ ቀስቃሽ ንግግሮችን በማድረግና የስራ ቅጥር ፈላጊዎች እንዴት ለቃለ-መጠይቅ መዘጋጀት እንዳለባቸው በማስተማር ከሚያገኘው ገቢ ላይ የኮሌጅ ትምህርቱን ወጭ ይሸፍን ነበር፡፡

የአሌክስ የሕይወት መርህ ቀላል ነው፡፡ “ራስህን መሆን ከፈለግህ በሌሎች አትተማመን፡፡ እውስጥህ ያለውን ፍላጎትና ህልም ዕውን ማድረግ ከፈለግህ ደግሞ ለሌሎች ጥሩ በመሆን አግኘው፡፡” የሚል ነው፡፡

በ1970ዎቹ መጨረሻ ዘ ካፔሎ ግሩፕ/The Capello Group አትላንቲክን አቋርጦ ስዊዘርላንድ የገባ ሲሆን በዚያም ከከአውሮፓና ከመካከለኛው ምስራቅ በርካታ ደንበኞችን ለመሰብሰብ ችሏል፡፡

“አንዳንዶች የባንክ ሥራ ገንዘብ ማግበስበስ ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ይህ የግንዛቤ ጉድለት ነው፡፡ በርግጥ ገንዘብም አንድ ነገር ነው፡፡ለኔ ግን ከሚገጥሙህ ያልታሰቡና አዳዲስ እንቅፋቶች ጋር መጋፈጥ፤ምሁራዊ ለዛህን እንዲሁም የሙያ ሥነምግባርህን ሳትለቅ መቆየት መቻል እና ይህን ሁሉ ስታልፍ ደግሞ ያን የተባለውን ገንዘብ ታገኛለህ፡፡ገንዘቡ የሚገኘው የምትፈልገውን እየሠራህ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ትኩረት ስላልነፈግኸው እና ጊዜ ስለቸርከው ጭምር ነው፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ልትደርስበት ያሰብኸው ራዕይ ሲኖር ብቻ ነው፡፡” የሚለው አሌክስ አከል አድርጎም “ፍላጎትህና ህልምህ በራሱ፤በራስ የመተማመን መንፈስ ይፈጥርልሃል፡፡ በራስ መተማመን ካለህ ደግሞ የምትሠራው ሥራ ከሰነቅኸው ግብ ሊያደርስህ እንደሚችል እምነት ያሳድርብሃል፡፡ማለት የስኬትን ደፍ መርገጥ የምትጀምረውም ይኼኔ ነው፡፡ ያኔ ደግሞ ለሌሎችም ትተርፋለህ፡፡” ይላል

አሌክስ ለሌሎች መሥራት ይችልበታል፡፡ለሁለት ጊዜያት የዓለማቀፉ Young President’s Organization/YPO ሊቀመንበር ሆኖ ሲመረጥም በስራው ያስመሰከረው ይኼንኑ ነው፡፡

ዋይፒኦ/YPO “ዓለማችን ምቹ እንድትሆን የሚጥር ድርጅት ነው፡፡እንደ ሊቀመንበር YPO ዓለማቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኝ ሠርቻለሁ፡፡አሁን YPO እና ስራው በመላው ዓለም ይታወቃል፡፡” የሚለው በኩራት እና በእርግጠኝነት ስሜት ሆኖ ነው-አሌክስ፡፡

አሌክስ ብዙ ጊዜውን ወደ ታዳጊ አገሮች በመጓዝ እና በእነዚህ ሃገሮች የሚገኙ ታዋቂ የቢዝነስ ሰዎችን በማሰባሰብ ለ YPO ዓለማቀፍ የወዳጅነት ግንኙነት መስመር ዘርግቶለታል፡፡ አሌክስ እንደሚለው YPO ይኼን የሚያደርገው ካፒታሊዝምን ወደ አዳጊዎቹ ሃገራት ገንቢና አዎንታዊ በሆነ መንገድ ለማስተዋወቅና በዚያም መልካም ፍሬ ያፈሩ ዘንድ ነው፡፡

አሌክስ እነዚህን ሃገሮች ብቻ ሳይሆን የ YPO ን አባላትም መርዳት አስፈላጊ እንደሆነ ያምናል፡፡ለዚያ ነው ግሎባል ሊደርሺፕ ኮንፈረንስ/Global Leadership Conference/ የሚባለውን ፕሮግራም ቀረጾ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው፡፡ይህ ኮንፈረንስ በዓለም ላይ ትላልቅ የቢዝነስ ሰዎችን ከሚሰበስቡት ስኬታማ ኮንፈረንሶች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡

አሌክስ በ YPO ቆይታው ከሃምሳ/50 በላይ አዳዲስ ቅርንጫፎች እንዲከፈቱ ትልቅ ሚና የተጫወተ ሲሆን ከነዚህ መሃልም በዱባይ በቤጅንግ በሞሮኮ በሳውዲት አረቢያ በፖርቹጋል በስፔይን በቼክ ሪፑብሊክ በፖላንድ በግብጽ እና በሩሲያ የተከፈቱት ይገኙበታል፡፡

አሌክስ ይኼን ስኬታማ ሥራ በአድናቆት በማስታወስ “አየህ ይህ የሚያሳየው ሰዎች ምንም እንኳ ቁጥራቸው ትንሽ ቢሆንም ፍላጎትና ተነሳሽነት ካላቸው ምን ያህል መስራት እንደሚችሉ ነው፡፡” ይላል፡፡

በ2006 ዓ/ም አሌክስ ላከናወነው ድንቅ ሥራ በ YPO እውቅና በማግኘት የ YPOን ትልቅ ሽልማት ግሎባል ሜምበርሺፕ/ሊደርሺፕ አዋርድ/Global Membership/leadership Award ለማግኘት የቻለ ሲሆን እሱ ከተሸለመም በኋላ የዚህ ሽልማት ስም በስሙ ተሰይሞ የአሌክሳንደር ካፔሎ አመታዊ ሽልማት/The Alexander Capello Annual Award/ ተብሏል፡፡

ከዚህ ጊዜ በኋላ አሌክስ ከ አርባ/40 በላይ በሚሆኑ የባንክ የመንግስት እና የግል እንዲሁም ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች ውስጥ የቦርድ አባል በመሆን አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ከነዚህ ድርጅቶች መሃል Cheesecake Factory; Geothermal Resources; California Republic Bank; RAND Russia Forum; City of Hope እና ALS Foundation በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

አሌክስ ለማህበረሰቡ በነጻ ለሚያከናውነው ተግባር እውቅናና ሽልማቶች አሁንም እየጎረፉለት ነው፡፡በመጨረሻም አሌክስ ምንም ዓይነት ህልም ስለሌላቸው ሰዎች እንዲህ ሲል ነግሮን ይሰናበተናል፡፡

“እነዚህ ሰዎች ሁሉም ነገር በእንቅስቃሴ ውስጥ ነው እንደሚባለው ይንቀሳቀሳሉ እንበል እንጅ  በቁም የሞቱ ናቸው፡፡ትልቅ ወይም በጣም ጥሩ ህልም ላትሰንቅ ትችላለህ፡፡ነገር ግን ህልም ሊኖርህ ይገባል፡፡ ኢንተርፕርነር የምትሆነው ግን ህልም ስላለህ ሳይሆን ይህን ህልምህን ለማሳካት መጣር ስትጀምር ነው፡፡ ጥረት ካደረግኽ ደግሞ ስኬታማ ሰው ትሆናለህ፡፡”

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.